History

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሃይማኖት አጭር ታሪክ

መግቢያ

ህዳር ፩ቀን ፪፻፲፮ ዓም (2023-10-01)
ውድ የደብረ ምጥማቅ ቅድስት ማርያም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቤተሰቦች ምዕመናን !!
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ክርስትና እምነት ለሃገራችን ለኢትዮጵያ ታሪክ ቅም አያት ሆና፣ ጉልላታዊ ታሪክ መሆኗ አሌ የማይባልበት እውነት ነው።የተዋሕዶ እምነትን የሁለት ሺ ዓመት ያልተቋረጠ ታሪካዊ አካሄድን መርምሮ ለተረዳ የተዋሕዶ እምነት ለኢትዮጵያ ያበረከተቻቸው እጅግ ብዙ ገፀ በረከቶችን ፈልጎ ያገኛል። ከብዙ በጥቂቱ ቢገለፁ:-
⦁ ሙሉ ትምህርትን ፣ቋንቋን፣ ፊደል መቅረፅን፣ሥነ ጽሑፍን ከጠባዩና ከሞያው ጋር አዋሕዳ ጥቅም ላይ እንዲውል ያደረገች፣
⦁ ሥነ ጥበብም ሆነ ኪነ ጥበብ ከዓይነቱና ከመልኩ ጋር አቀነባብራ ያቀረበች፣ ታሪክን ሸክፋ ይዛ ባህልን እና ጥንታዊ ቅርሶችን ጠብቃና ተንከባክባ ለትውልድ ያቆየች፣
⦁ ነፃነት በአንድነት በፍቅር ኢንዲገማመድ አድርጋ በማቆራኘት ጀግኖችን ፈጥራ አገርን ከነድንበሩ ሕዝብ ከነክብሩ እንዲጠበቅ በማድረግ ግንባር ቀደም ሚና መጫወት ብቻ ሳይሆን የአርበኝነት ገድል የፈፀሙ ልጆቿን በተክለ ስውነታቸው ከፊት ተርታ እንዲሰለፉ አድርጋ የአገር ፍቅር ማለት ዋጋ የማይወጣለት ትልቅ ትርጉም ያለው መሆኑን በተግባር ያሳየች፣የአባታችን የአቡነ ጴጥሮስን የቆራጥ የአርበኝነት ሕያው ታሪክን መመልከት በቂ ነው።
⦁ከእኔ እምነት ሌላ ሌላው ወበከንቱ ነው ሳትል፣የሌላውንም ሃይማኖት አክብራና አስከብራ ለተከባብሮ መኖር ለዓለም ተምሳሌት በመሆን በተግባር ያሳይች። ልዩነትን ይዞ በፍቅር አብሮ ጎን ለጎን መኖርን በተግባር ላለፉት ሺ ዓመታት በተግባር ያሳየች
⦁ የእምነትን ውስጠ ሚስጥር በፍልስፋና ገለፅለፅ በማዳረግ ያስረዳች፣ ወዘተ፣ወዘተ ተዘርዝሮ የሚያልቅ አይደለም።
ይህን ተዝቆ የማያልቅን የቤተ ክርስቲያንን ታሪካዊ ገድል በተቻለ መጠንም ማወቅ ግድ ነው። እሳት ሆኖ ያለማቃጠል፣ ውኃ ሆኖ ያለርጥበት አይቻልም እንደሚባለው ሁሉ ነፍስም በተፈጥሮዋ እንዳታውቅ ሆና ስለአልተፈጠርች ተዋሕዶአዊ ሆኖ ተዋሕዶን አለማወቅ መሆን የሌለበት በመሆኑ የተዋሕዶን እውቀት መሻት ግድ ነው።
እውቀትም ክሂል/ችሎታ በመሆኑ የዕርጋታ ጊዜን ወስዶ የመንፈስ ፀጥታን ይዞ ወደዚያ ማዘንበል ፍፁም ነው። እውቀት ብቃትን ስለሚያስጨብጥ እያንዳንዱ ምዕመን ታሪኩን ማወቅ፣ ያወቀውም በየጊዜው እውቀቱን እያዳበረ መነሻውን እና መዳረሻውን አውቆና ተገንዝቦ በብቃት ቤተ ክርስቲያኑን መጠበቅ መንከባከብ ቃለ ሕይወታዊ ትምህርሕቷን ማስረፅ ግድ ነው። ይህ ሆኖ ሲገኝም ነው የታሪክ ቅብ ብሎሽ ሊኖር የሚችለው።
በተለይም ያለንበት ክፍለ ዘመን የእውቀት ዘመን በመሆኑ ሁሉን ነገር በእውቀታዊ ብቃት ማደራጀት ግድ ሆኗል።መሆን ብቻ ሳይሆን ስኬታማነትን፣እውነተኛ ደስተኛሰው ከመሆን ባሻገር የስብዕና ልህቀትን በተለይም መንፈሳዊነትን መጎናፀፍ የሚቻለው በዚህ መንገድ ብቻ ነው። አለበለዚያ ግን ለነፍስ ወይ ለስጋ ያልሆነ ውሃውን አድርቆ አሣውን መጭረስ እንዳይሆን ከወዲሁ ሊታሰብበት የሚገባ ቁም ነገር አዘል ተግባር ነው።
ለዚህም ነው የደብረ ምጥማቅ ቅድስት ማርያም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሉንድ መጽሔት ቦርድ ይህን ሀላፊነት ለመወጣት ይቻለው ዘንድ የእውቀት ዘመቻ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ አጠንክሮ ለመስራት ሰፋ ያለ ዝግጅት ይዞ የወጣው። እነሆ የእውቀቱ ማዕድ ተካፋይ ሁኑ ብሎ ጥረቱን ስራዬ ብሎ የተያያዘው።
ይህንንም አካሄድ ተግባራዊ ለማድረግ ይቻለው ዘንድ በመፅሔት ቦርዱ ዙሪያ ልሂቃንን፣ ምዕመናንን አስተባብሮ እና ተመካክሮ ጠንከር ያለ ራሱን ችሎ ከቃለ ዓዋዲው ውጪ ወይፍንክች የማይል ጠንካራ ውሳኔ የመስጠትና በአመክንዮአዊ የውሳኔ እርምጃ የመውሰድ አቅም ያለው መጽሔት ቦርድ ሆኖ የወጣው።መልዕክቱም ለምዕመኑንም ሆነ ለሚመለከታቸው በሙሉ ተዳርሷል። የምዕመናኑም ምላሽ አበረታቺ ሊሆን ችሏል።ሆኖም ግን ምዕመናኑ በርቱ ይበሉ እንጂ:-
“ዘግይታችኋል። ጨርሳችሁ ሳትጠፉ ከመረጥናቹሁ፣ ድሕረ ገፁን ካስተዋወቃችሁን ከረጅም ጊዜ በኋላ አሁን ብቅ ማለታችሁ ይሁና የሚያሰየኝ ነው። እስቲ አሁን የምትሉንን ሂዱት እና ወቀሳውም ሆነ ምስጋናው ከዚያ በኋላ ይሆናል” ብለውናል።
የደብረ ምጥማቅ ቅድስት ማርያም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ ክ በሉንድ መጽሔት ቦርዱም ከዚህ የምዕመናኑ ፈጣን ምላሽ በመነሳት ድሕረገፁን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በማንቀሳቀስ ንቁ ተሳትፎን በስፋት ጀምሯል።በጀመረው መድረክ ላይም የምዕመናኑ ምላሽ ከገመትነው በላይ ሆኗል።
ካህናትን አስመልክቶ የካህናቶቻችን ተቀዳሚ ተልዕኮ ምእመናንን ለምስጢራተ ቤተ ክርስቲያን ሱታፌ ማብቃት ነው። ምእመናን በክርስቲያናዊ ሕይወት ፀንተው በመቆየት ለሥጋ ወደሙ አብቅቶ ለሰማያዊው ሕይወት ማዘጋጀት ማለት ነው። ጌታችን መድሐኒታችን እየሱስ ክርስቶስ ከትንሣኤው በኋላ በቅዱስ ጴጥሮስ አማካኝነት ለካህናት ያስተላለፈው መልዕክት “ግልገሎቼን፣ ጠቦቶቼን ጠብቁልኝ፣ በጎቼን አሠማሩልኝ” ብሎ በካህናት ላይ ከባድ አደራ የጣለበት የካህናትን/ የአገልጋዮችን ኃላፊነት በሚገባ አስገንዝቦ በተግባር የእረኝነት ተግባራቸውን ይወጡ ዘንድ ያሳሰበበት ነው።
የደብረ ምጥማቅ ቅድስት ማርያም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በሉንድ መጽሔት ቦርዱም ካህናት ምእመናንን በአጸደ ቤተ ክርስቲያን እንዲያሰማሩ ሲሾሙ የተጣሉባቸው ግዴታዎች ይህንን ግዴታ ለመፈጸም የተሰጣቸው ሥልጣን ከተጠያቂነት ጋር እንደሆን በቅዱሳት መጻሕፍት ተዘርዝሯል የተቀመጠ የማያወላዛ መልዕክት መሆኑን ለካህናቱም ለማሳተማር ሳይሆን ለማስታወስ ትኩረት ሰጥተን መጽሔት ቦርዱ በሰፊው ይሰራበታል።
የደብረ ምጥማቅ ቅድስት ማርያም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ክርስቲያን በሉንድ መጽሔት ቦርዱም ንቁ ተሳትፎን ለማድረግ ሲነሳ ለብቻው አልተነሳም።ባለፈው አንድ ወር ውስጥ ብቻ ሕይወታቸው በመለኮታዊው እስትንፋስ የተሞላ የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንትን፣ አውቀት ጠገብ የተዋሕዶ ምሁራንን መጽሔት ቦርዱ አግኝቶ ሀሳቡን በደንብ ገልፆላቸዋል። እነሱም ከያሉበት በአንድ ቃል የእግዚአብሔር ቸርነት ይጨመርበት፣ የድንግል ማርያም አማላጅነትን አይለየው፣ የሃይማኖታችን ተክል የሆኑት የአቡዬ መንፈስ አይለየን ልፋታችንን ያግዘው ይባርከው ብለው ሊተባበሩት ቃል ገብተው የአዎንታዊነት መልስ ሰጥተዋል። መልስ መስጠት ብቻ ሳይሆን በቀጥታ ወደ ተግባር በመተላለፍ የተኙ ነፍሶችን እንዲነቁ የማድረጉን ተልኳቸውን ውለው ሳያድሩ ተያይዘውታል።
የደብረ ምጥማቅ ቅድስት ማርያም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ክርስቲያን በሉንድ መጽሔት ቦርዱም በአጠቃላይ በሀገሪቷ በተለይም በምንኖርበት በስኮነ አካባቢ ሊቃውንትን እና አስተዋይ ልቦና ያላቸውን ምዕመናንን የማገለል አካሄዶች በማቆጥቆጥ ላይ መሆኑን በግልፅ ተገንዝቧል። ይህን ለማስቆም ወደ ምዕመናን ትኩረትን መጣል መሆኑ ቦርዱ ብቻ ሳይሆን ሁሉን ያስማማ ሀሳብ ሊሆን ችሏል።
በመሆኑም ይህን በተግባር ለመተግበር የመፅሔት ቦርዱ የተሰጠው ተልዕኮ ሕይወታቸው በመለኮታዊው እስትንፋስ የተሞላው የቤተ ክርስቲያን የሊቃውንቱን እውቀት ማስፋፋት ብቻ እና ብቻ ነው። ይህንንም ለማድረግ በመጀመርያ ምዕመን ተኮር የሆነ ስርዓትን መመለስ፣ ብሎም እውቀትን ማስረፅ ነው። እውቀት ከሰረፀ ደግሞ አጓጉል ሃይማኖት አይሉት የቶፋ ማውደልደል ወይ ሌላ ስነልቦናን ቆፈን አስይዞ በፍርሃት ሰውን ለሚያስጨንቅ ድርጊት ሰለባ ከመሆን ምዕመናንን ማንቃት ማለት ነው።
ይህንንም ለማድረግ በመጀመርያ ከሁሉ ነገር ቀዳሚነት የሚኖረው ማንነትን ማስጨበት ብሎም የእውቀትን አድማስ ማስፋት ከሚል መርሆ መነሳት ነው። የመጽሔት ቦርድ መነሻውም ታሪክን ማወቅ ወሳኝ ነው ብሎ ያምናል። ታሪክ በተለይም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ጉልላታዊ ታሪክ ለተጭነቀ ጭንቅላት ፍቱህ መድሐኒት ነው የሚለውን ሙሉ በሙሉ የሚቀበለው ሀሳብ ነው።
ስለሆነም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ታሪካዊ መሰረትን በጣም በአጠረ መልኩ ለመንደርደርያ ያክል ከዚህ መግቢያ ቀጥሎ በቅርቡ በድሕረ ገፁ ላይ ያወጣል። ከብዙ በጥቂቱ የቤተ ክርስቲያናችንን ሥርዓት፣ ትምሕርት፣የቤተ ክርስቲያናችንን አስተዳደር እና ተግሣጽ፣ ቃለ ዓዋዲውን የዕለታት የአውራኀ እና የዓመታት አቆጣጠር በጥልቀት ያጠናል። የጥናቱንም ውጤት በድሕረ ገጹ ላይ አውጥቶ ያወያያል። የበቁት ሊቃውንቱ የመንፈስ አባቶቻችን በበኩላቸው ልዩ ልዩ ፍልስፍናዎችን፣ ስለ ሥነ ፍጥረት፣ስለ ስብዐቱ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን፣ ምስጢረ ሥላሴ፣ ምስጢረ ሥጋዌ፣ምስጢረ ጥምቀት፣ምስጢረ ቁርባን፣ምሥጢረ ትንሣኤ ሙታን ወዘተ ወዘተ በተቻለ መጠን ድሕረ ገፃችንን በብዛት በመጠቀም በሠፊው ያሰተምሩናል።
የደብረ ምጥማቅ ቅድስት ማርያም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ ክርስቲያን በሉንድ መጽሔት ቦርዱም ሊቃውንቱ ሊተባበሩን ቃል በገቡልን፣ የመንፈስ አባቶች በረዱን፣በተባበሩን መጠን ኃይማኖት እና እምነት ነክ በሆኑት ትምሕርቶች ላይ ለመስራት ወደ ምዕመናን በድሕረ ገፃችን፣ በመፅሔቶቻችን አማካኝነት ለማድረስ ቅድመ ዝግጅቱ አጠናቆ ወደ ተግባር ተሰማርቷል።
የደብረ ምጥማቅ ቅድስት ማርያም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሉንድ መጽሔት ቦርድ ዝግጅት የሚሸፍነው ታሪክን ማወቅ ማሳወቅ፣ የጥናት ጉባኤዎችን ማዘጋጀት ማደራጀት፣ ዜና ቤተ ክርስቲያንን በአጥቢያ፣ በሀገር(ስዊድን) ፣ በኢትዮጵያ፣ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ያሉትን ዜናዎች ለአጥቢያ ቤተ ክርስቲያ ምዕመናን ማድረስ። እንደዚሁም ጉልበት በፈቀደ መጠን ስለ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለባእዳን ግለሰቦች፣ ቤተ ክርስቲያናት፣ ተቋማት በስዊድንኛ እና በእንግሊዝኛ ተደራሽነት የሚኖረው አውታረ መረብ ዘርግቶ ማዳረስ።
የአለም ሁሉ መድኃኒት ቸር የሆነው ቸሩ መድኃኒአለም በጎደለ ይሙላበት !!!!
የደብረ ምጥማቅ ቅድስት ማርያም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሉንድ
መጽሔት ቦርዱ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሃይማኖት አጭር ታሪክ

የተዋሕዶ ዕምነት በመጀመርያ ወደ ኢትዮጵያ የገባው በመጀመርያው ምዕተ ዓመት(First century) ላይ ነው። ይኸውም ከክርስቶስ ልደት በኳላ በ፴፬ኛው ዓመተ ምህረት ገደማ መሆኑ በብዙ የታሪክ መዛግብት ላይ ሰፍረው ይነበባሉ።በክርስትና ታሪክ ውስጥ ዘመነ ሐዋሪያዊ ( Time of the Apostles) ተብሎ የሚጠራው የአስራ ሁለቱ ሐዋርያት ሐዋርያዊ ተልእኮ ከጀመረበት እና ጌታችን መድሐኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሦስት መዓልት እና ሦስት ሌሊት በከርሰ መቃብር ቆይቶ ከተነሳበት ዕለት ጀምሮ እስከ መጨረሻው ሐዋርያ ሞት(ዮሐንስ ወልደዘብዴዎስ በ ፺፭ ዓም ገደማ) ድረስ ያለው ጊዜ ዘመነ ሐዋሪያዊ ተብሎ ይጠራል። በዚህም ወቅት ነበር የኢትዮጵያ ኃይማኖታዊ ዕምነት ከይሁዳዊነት (Jews) ወደ ሐዋርያዊ(Apostolic) የክርስትና እምነት በመሳፍንቱ (Royalist)፣ በንግስቲቷ ቤተ መንግሥት አካባቢ መለወጥ ሀ ብሎ የጀመረበት ወቅት ተብሎ በታሪክ የተረጋገጠው።

የ፲፪ቱ (12) ሐዋርያት ስም ከዚህ በታች የተዘረዘሩት ናቸው
፩:- ጴጥሮስ (ስምኦን ወይም ኬፋ)
፪:- እንድርያስ እኅሁ ለጴጥሮስ
፫:- ያዕቆብ ወልደዘብዴዎስ
፬:- ዮሐንስ ወልደዘብዴዎስ
፭:- ፊሊጶስ
፮:- በርተለሜዎስ
፯:- ቶማስ ዘህንደኬ ዲድሞስ
፰:- ማቴዎስ (ቀራጭ የነበረው)
፱:- ያዕቆብ ወልደእልፍዮስ
፲:- ታዲዎስ (ልብድዮስ)
፲፩:- ስምዖን ቀነናዊ (ናትናኤል)
፲፪:- የአስቆሮቱ ይሁዳ (በማትያስ ተተክቷል)’

ጸሎተ ሀሙስ

የክርስትና እምነት ወደ ኢትዮጵያ መች ገባ ?
የክርስትና እምነት ወደ ኢትዮጵያ መች ገባ ለሚለው የታሪክ ሂደት እንደ ማጣቀሻ ሆኖ የሚቀርበው በመፅሐፍ ቅዱስ(የሐ። ሥ ምዕራፍ ፰)ላይ ተቀምጦ ያለው የኢትዮጵያ ንግስት ገርሳሞት (፯ኛ) ወይንም በብዛት በምትታወቅበት የንግስት ሕንደኬ በጅሮንድ የነበረው ባለስልጣን ወደ ኢየሩሳሌም ሄዶ ከተጠመቀበት ታሪካዊ፣ቅዱስ ቀን ጀምሮ ነው።

ይኸውም በዚህ ምዕተ ዓመት ላይ የኢትዮጵያ ንግስት የነበረችው ንግስት ገርሳሞት ፯ኛ/ሕንደኬ(Kandake/Candace queen of the Ethiopians)በፍልስጥኤም/ፓላስትና (Palestine) አውራጃ በጋዛ የሚቀመጥ አንድ ተወካይ ከፍተኛ ባለስልጣን በጅሮንድ (የገንዘብ/ የንብረት ጉዳዮች ሀላፊ የሆነ ከፍተኛ የመንግስት ሹም) አስቀምጣ ነበር። ይኸው የንግስቲቱ ተወካይ በጅሮንድ/ ጃንደረባ ለስግደት ወደ እየሩሳሌ ሄዶ ስግደቱን ጨርሶ በመመለስ ላይ ሳለ በእግዜር ጥበብ እና መልካም ቸርነት ለክርስትና መብቃቱ መፅሐፍ ቅዱስ(የሐ። ሥ ምዕራፍ ፰ ቁጥር ፳፯) በግልፅና በማያሻማ መልኩ ቁልጭ አድርጎ ማስረዳቱ እውነተኛ ታሪክ መሆኑን ያረጋገጠ ነው።

በዚህ ቀን “የጌታ መልአክ በጌታ ትዕዛዝ መሰረት ዲያቆኑ ፊልጵስን “ተነሥተህ በደቡብ በኩል ከኢየሩሳሌም ወደ ጋዛ ወደ ሚያወርደው ምድረ በዳ ወደ ሆነው መንገድ ሂድ” (የሐዋ ሥራ ም፰ ቁ ፳፮) ብሎ ባዘዘው መሰረት ዲያቆኑ ፊልጵስም ወደ ታዘዘው ስፍራ ሄዶ በጅሮንዱን በማጥመቁ ምክንያት የኢትዮጵያ የክርስትና እምነት ሀ ብሎ በዚያች ቀን ነው የጀመረው የሚለው ታሪክ የብዙ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ፀሐፊዎችን ያቀራረበ የታሪክ ሊቃውንቱንም ያስማማ ታሪካዊ መነሻ ነው።
ይህ የመፅሐፍ ቅዱስ ምዕራፍ (የሐ። ሥ ምዕራፍ ፰ ቁጥር ፳፯) ገለፃ ያካተተው ሌላው ታሪካዊ ቁም ነገር ቢኖር የኢትዮጵያ ንግስት የነበረችው የንግስት ገርሳሞት ፯ኛ/ሕንደኬ በጅሮንድ ለስግደት ወደ ኢየሩሳሌም መሄዱ ነው። ስግደት በወቅቱ በይሁዳ እምነት ተከታዮች ዘንድ መለያቸው ነበር። ይህ ማለትም ጃንደረባው ክርስትናን ከመቀበሉ በፊት የጥንተ ስብከት የይሁዳ እምነት አራማጅ እንደነበረ ማየትን ሲያስችል የመጣባትም ሀገረ ኢትዮጵያም የይሁዳ እምነት አራማጅ እንደ ነበረች ማስረጃ ይሰጣል።
ኢትዮጵያ ክርስትናን ከመቀበሏ አስቅድሞ የኦሪትን ህግ የተቀበለች ስለነበር ዓመተ ዓለምን ወደታች እየቆጠረች የጌታን መወለድንም በተዐምራዊ መንግድ ትጠባበቅ ሰለነበርም ክርስትናን ለመቀበል አመቺ ሁኔታ ላይ ነበረች ማለት ይቻላል። የኢትዮጵያ ንግስት በጅሮንድም ወደ ኢየሩሳሌም ወርዶ ከስግደቱ መልስ በመንገድ ላይ ዲያቆኑ ፊሊጶስ አግኝቶ ሲያጠምቀው በመንፈስ በመመረጡ ምክንያት መሆኑ በቀላሉ ሆኔታው አስረጂነት ያለው ነው።
ይህ ማስረጃም እንዳንድ ሀገራትም ይሁኑ ተራኪ ግለሰቦች ወደ ታሪክ ሽሚያ በመሄድ በጅሮንዱ ኢትዮጵያዊ”አይደለም”ለማለት ሞክረው ታሪክ ያሳፈራቸውም በጣት የሚቆጠሩ ወገኖች አልጠፉም። ለዚህ የታሪክ ሽሚያቸው እንደ መከራከሪያቸው አድርገው ያቀርቡ የነበረውም ንግስት ገርሳሞት ፯ኛ/ህንደኬ የኢትዮጵያ ንግስት ሳትሆን የሜሪዋ/ኑብያን ነበረች በማለት ነው።
ለዚህ ስህተታቸው ምክንያት የኢትዮጵያን መልክዓ ምድር አቀማመጥን ከሱዳን ጋር በማምታታ ነው። የመልክዓ ምድር አቀማመጥን ጉዳይ ማንም ሊስተው በማይችለው መልኩ ያስቀመጠው አሁንም በድጋሚ የታላቁ መጽሐፍ ቅዱስ ትንተና ነው። ዘፍጥረት ምዕራፍ ፪ ቁጥር ፲ ላይ እንዲህ ይላል
‹‹የሁለተኛው ወንዝ ስም ግዮን ነው። እርሱም የኢትዮጵያን ምድር ሁሉ ይከብባል”
ግዮን የሚለው አባይ መሆኑ ብዙም የጂኦግራፊ ሊቅ መሆኑን የሚጠይቅ አይደለም። ይህን መሰረታዊ መረጃ ተይዞ ዛሪ ያለንባት ኢትዮጵያመሆኗየሚያጠራጥር አይደለም።
ይህንኑ የይሁዳ እምነት ታሪክ የኢትዮጵያ ክብረ ነገስት መፅሐፍ ”ቀዳማዊ ምኒልክ ወደ ኢየሩሳሌም ተጉዞ በጥበቡና በእውቀቱ በባለጠግነቱ ስሙ በዓለም ሁሉ ከታወቀው አባቱ የዳዊት ልጅ ንጉስ ሰለሞንን ተዋውቆ ለሶስት ዓመታት ያክል ከአባቱ ዘንድ በኢየሩሳሌም ከቆየ በኋላ በአባቱ በንጉስ ሰለሞን ተመርቆ እና መልካም ፈቃድ ብዙ የንጉስ ሰለሞን የመኳንንት ልጆችና የኦሪት ካህናት ፅላተ ሙሴን ይዘው ቀዳማዊ ምኒልክን አጅበው ወደ ኢትዮጵያ እንደመጡ ይናገራል።
ከዚህ ጊዜ በኋላም የይሁዳ እምነት ወደ ኢትዮጵያ ገብቶ በሰፊው እንደ ተስፋፋ መፅሐፉ ያስረዳል። መረጃዎችንም ቀረብ ብለን ስንመለከታቸው:- የበጅሮንዱ መጠመቅን አስመልክቶ በመፅሐፍ ቅዱስ በሐዋርያት ስራ በምዕራፍ ፰ ከቁጥር ፳፮ እስከ ፴፱ ላይ የሚከተለው ሰፍሮም ይገኛል፡፥
”በጅሮንዱም በእየሩሳሌም ያደረገውን ስግደት አጠናቆ ወደ ቤቱ በሰረገላ ውስጥ ተቀምጦ በመመለስ ላይ ሳለ የኢሳይያስን (the Book of Isaiah the prophet) መፅሐፍ እያነበበ ነበር። በዚህም ወቅት ከውጪ በኩል አንድ ድምፅ ይሰማል። ድምፁም የወንጌላዊው የፊሊጶስ ነበር። የድምፁም ይዘት “እውን ይህ አያነበብከው ያለኸውን ቃል በቅጡ እየገባህ ነው እን ?” የሚል ነበር።
በጅሮንዱም ፈጥኖ በመመለስ “እንዴት አንድ የሚተረጉምልኝ የሚገልፅልኝ ሰው ሳላገኝ ከቶ እንዴት ሊገባኝ ይችላል?” በማለት በቅንነት እንዳልገባው መለሰለት። መልሶለትም ወንጌላዊው ፊለጵስ ወደ ሰረገላው ወጥቶ ከእርሱ ጋር ይቀመጥ ዘንድ ተማፀነው። እያነበበ ያለውን ትርጉሙን እና መልዕክቱ ዘርዝሮ እንዲገልፅለት ወንጌላዊው የፊሊጶስን በትህታትና ይማፀነዋል። በጅሮንዱም እያለበበው የነበረው እና ለመረዳት አዳግቶት የነበረው የመጽሐፉ ክፍል ይህ ነበረ፤-
“እንደ በግ ወደ መታረድ ተነዳ፥ የበግ ጠቦትም በሸላቹ ፊት ዝም እንደሚል፥ እንዲሁ አፉን አልከፈተም።በውርደቱ ፍርዱ ተወገደ፤ ሕይወቱ ከምድር ተወግዳለችና ትውልዱንስ ማን ይናገራል”
የሚለውን በጅሮንዱ እባክህ ነቢይ ሆይ ይህ ስለ ማን ይናገራል? ስለ ራሱ ነውን ?ወይስ ስለ ሌላ? ብሎ ጠይቆታል።
ወንጌላዊው ፊልጶስም ስለ ክርስቶስ የተፃፈውን የኢሳይያስን ትንቢት ትርጉሙን በደንብ ገልፆለት በሰፊው የኢየሱስ ወንጌል ወደ በጅሮንዱ ውስጥ ጠልቆ እንዲገባ አድርጎ ሰበከለት ገለፀለት። ይህንንም ስብከት በሰፊው እና በጥልቀት ወደ ውስጡ እስኪዘልቅ ድረስ በደንብ እየገለፀለት አበረው ብዙ ከተጓዙ በኳላ ወደ አንድ የኩሪ ውሃ አጠገብ መድረሳቸውን በጅሮንዱ ይመለከታል። ባገኘው ሃይማኖታዊ ትምህርት እና ሃይማኖት ተመስጦ ፈጥኖም ፊሊጵስን ተጨማሪ ጥያቄ በጅሮንዱ ይጠይቀዋል።
ጥያቄውም “እነሆ ውኃ ከዚህ አለ!! እንዳልጠመቅ የሚከለክለኝ ምንድር ነው?” የሚል ነበር። ፊሊጶስም ሲመልስለት በፍጹም ልብህ ብታምን፥ የሚፈቀድልህ ነው ተፈቅዶልኸልም አለው። በጅሮንዱም በፍፁም መንፈሳዊነት ተሞልቶ ስለነበር “ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ አምናለሁ” አለ። ይህን ፍፁም እምነታዊ ቃሉን በታአማኒነት ለወንጌላዊው ለፊሊጶስ ስጥቶ የሰረገላው ነጂ ሰረገላውን ያቆም ዘንድ በጅሮንዱ አዘዘ። ሰረገላውም እንደቆመ ወንጌላዊው ፊልጶስና በጅሮንዱ ሁለቱም ከሰረገላው ወርደው ወደ ውኃው በመሄድ ወንጌላዊው ፊሊጵስ ኢትዮጵያዊውን በጅሮንድ በመንፈስ ቅዱስ ጠምቆት ከክርስቶስ ጋር አንድ አድርጎት ከኃጢዐት ለይቶት አዲስ ሕይወትን እንዲኖር አድርጎት ከውኃውም ከወጡ በኋላ ከመቅስፈት የጌታ መንፈስ ፊልጶስን ከበጅሮንድ ጎን በተዐምር ነጥቆ ወሰደው።
እዚህ ላይ የስም መደራረብ ስለ አለ ይኽኛ በጅሮንዱን ያጠመቀው ለኢየሩሳሌም ማኅበር አገልግሎት ከተመረጡት ከሰባቱ ዲያቆናት አንደኛው ፊልጵስ ነው። እንጂ ፊልጵስ ሐዋርያው እንዳልሆነ ልብ ሊባል ይገባል።

ኢትዮጵያዊው በጅሮንድ

ኢትዮጵያዊው በጅሮንድም ከዚያ ተዐምራዊ ሁኔታ በኋላ ወንጌላዊው ፊልጶስን ደግሞ አላየውም። እነሆ ውስጡ በደስታ፣ በፀጋ እና በመንፈሳዊነት ተሞልቶ ፊቱን ወደ አገሩ አቅንቶ ጉዞውን ቀጠለ። በዚህ ተዐምራዊ ክስተትም ምክንያትም :- “ከኢትዮጵያ ወንዝ ወዲያ ማዶ የሚሰግዱልኝ የተበተኑት ልጆቼ መባዬን ይዘው ወደኔ ይመጣሉ” የሚለው ትንቢት በዚ ህ በጅሮንድ ጥምቀት ምክንያት ተፈጸመ። በዚህ መለኮታዊ ሁኔታ የሰላም፣የፍቅር፣የአንድነት ባለቤት የሆነው ክቡር እግዚአብሔር በፍፁም እና በልዩ ክብር በበጅሮንዱ አማካኝነት ኢትዮጵያን ቀደሳት ሕዝቧንም በሥጋ፣በነባቢት ነፍስ፣በደመ ነፍስ ሕያውነት አምላክ አጎናፅፋት።
ከዚህ ታሪካዊ መሰረት ለሚነሳም የኢትዮጵያ ኦቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጥንታውያን አብያተ ክርስቲያናት ከሚባሉት ተርታ እንደምትመደብ መመደብ ብቻ ሳይሆን በአምላክ ልዩ ትዕዛዝ ከእግዚአብሔር አፍ በወጣች ለሕይወት መንፈስ የተመረጠች ከተፈጥሮ ጠባይዕ የማትቆጠር ሟች ያልሆነች የእግዚአብሔር የቤቱ አምድ ሆና የሕይወት መንፈስ የታደለች ኢትዮጵያ ናት። ይህ ደግሞ ከቶ አሌ ሊባል የማይቻል የታሪክ አሻራ ነው። በመንፈስ ቅዱስ መሪነትም የእምነቷ፣ የትምሕርቷ እና የሥርዓቷም መሰረት የሐዋርያት እና የ፫፻፲፰ቱ ሊቃውንት ትምህርት መሆኑ በቀላሉ ሊገኙ የሚችሉት መረጃዎች እና ማስረጃዎች የሚያረጋግ- ጡት ነው።
የኢትዮጵያ ኦቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከ፭ቱ የምስራቅ አርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት አንድዋ ስትሆን የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ጉባኤ እና የመላው አፍሪካ አብያተ ክርስቲያናት አንድነት ጉባኤ መስራች ከሆኑት መካከል ግንባር ቀደም እናት ቤተ ክርስቲያን መሆኗ የተረጋገጠ ነው። ፍሬያማነትዋም ባላት የትምህርት ስልቷ፣ እውነታዊ ይዘቷ ከዓለም አቀፋ መንፈሳውያን ሊቃውንት ዘንድ እውቅናን የተቸረች መሆኗ እውቅ ነው።
ኢትዮጵያ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነትን በትምህርት ብሎም በጥምቀት ወዳና ፈቅዳ የክርስትናው መዓከል ወደሆነችው ወደ ቅድስቲቷ ኢየሩሳሌም በመሄድ ትቀበል እንጂ ማንም ኃይል በሰይፍም ይሁን በስብከት የጫነባት አይደለችም። ይህ በመሆኑም በጥንተ ስብከት ዘመን የነበሩትን አይሁዳውያንንም ሆነ የአሕዛብን ሥልጣኔም ሆነ ቋንቋ ለመለወጥ የተነሳችበት ይሄ ነው ሊባል የሚያስችል አካሄድ ሄዳ የታየበት በታሪክ አልተመዘገበም። ውዴታን እንደ መሰረታዊ ኃይማኖታዊ ፍልስፍናዋ በማድረጓ በውዴታ ለሚሻ ሁሉ የሕይወት ቃልን ሁሉም በሚሰማው ቋንቋ የአገሩም ስልጣኔ በሚፈቅደው መሰረት ስታስተምር ኖራለች።
ከዚህ በጅሮንድ ክርስትናን ከመቀበል በፊት ኢትዮጵያ ብሉይ ኪዳንን ለመቀበሏ ተጽፈው ያለ ታሪኮች፣ትውፊቶች ልምዶች ባሻገር በሕዝብ የ አኗኗ ዘይቤ፣አያሌ ልምዶች፣ባሕሎች እጅግ ዘልቀው በመግባት እነሆ እስከዛሪ በሠፊው የሚታዩ ናቸው።እነዚህም የብሉይ ኪዳን ልምዶችና ባሕሎች በተዋሕዶ እምነት ውስጥ በዶግማ ወይንም በቀኖና ሳይሆን በልማድ ተጠብቀው ያሉ ናቸው።
ለናሙና ያክልም በብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ውስጥ እንዳይበሉ የሚከለከሉ እንስሳት እና እፅዋት ዛሪም የኢትዮጵያ ተዋሕዶ ተከታዮች አይመግቧቸዋል። ግርዛት በሀገራችን ከብሉይ ኪዳን በተወረሰው ልማድ መሰረት ወንድ ልጅ ሲወለድ ይገረዛል።ይህም የሕግ ሳይሆን የእያንዳንዱ ቤተሰብ የመልካም ፈቃደኝነት ውሳኔ ነው። ከዚያ በዘለለ የኦርቶዶክስ ተከታዮች ላይ ቤተ ክርስቲያኒቷ በግዴታ የምትጭንባቸው አንዳችም አይነት ግዳጅ የለም።
እዚህ ላይ ጎላ ጎላ ያሉትን ክስተቶች ለማንሳት ያክል ጠቀስናቸው እንጂ በኅዘን፣ በደስታ፣በባዓላት አከባበር፣የቤተ ክርስቲያን ውስጥ የማኅሌት ሥርዓት፣የካህናቱ ልብሰ ተክህኖት፣ ካባው፣ድርቡ፣ጸናጽኑ፣ከበሮው፣ኩፋሩ፣መጠምጠሚያው፣ የታቦቱ ክብር እና ሥርዓቱ ወዘተ ከብሉይ ኪዳን ሥርዓት ሲወርድ ሲዋረድ መጥቶ እነሆ አሁንም በግልጋሎት ላይ ያሉ ናቸው።

ይቀጥላል !!!